የሀገር ውስጥ ዜና

ከ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት የፕላስቲክ ቧንቧ አምራች ኩባንያ ስራ ጀመረ

By Shambel Mihret

November 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ከ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ኢ ዜድ ኤም ኩባንያ ተመርቆ ስራ መጀመሩን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የፕላስቲክ ቧንቧና መሰል የግንባታ ግብዓቶችን የሚያመርተው ኢ ዜድ ኤም ኩባንያ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ3 ሺህ ስኩዌር ሜትር የማምረቻ ሼድ ላይ ያረፈ ሲሆን÷ ከ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ÷ ከአዳማ ከተማ ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ እና ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን ኩባንያውን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ኩባንያው “ኢ ዜድ ኤም ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት” የተባለ ሲሆን”÷ ሪፎ ኢንተርናሽናል ከተሰኘው የቻይናው የፕላስቲክ ቧንቧ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ጋር በሽርክና ተቋቁሞ በዘርፉ የሚስተዋለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት አላማ በማድረግ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር ይሆናል ተብሏል፡፡

አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ግዙፍ 13 የኢንቨስትመንት ማዕከላት አንዱ መሆኑንም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የተገነቡ 19 የማምረቻ ሼዶች በጃፓን፣ በቻይና ፣ በሕንድ፣ በኖርዌይ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ተይዘው ከ8 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል ተብሏል፡፡