አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ውይይት በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል ያለውን በመቻቻል፣ መግባባትና መከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ያስቀጠለ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ውይይትን በተመለከተ የውጭ ፖሊስ አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ÷ በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን አንስተዋል፡፡
በሁለትዮሽ ጉዳዮች ውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና ጀርመን መካከል ያለውን መልካምና ሚዛንን የጠበቀ የትብብር ግንኙነት በይበልጥ ማሣደግ በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል ነው ያሉት፡፡
ጀርመን ኢትዮጵያ ውስጥ የምትሰማራበቸው የልማት አማራጮች በውይይቱ መለየታቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፥ በተለይም በኃይል አቅርቦት እና ማዳበሪያ ዙሪያ መሰማራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል ብለዋል፡፡
በንግድ ረገድም የኢትዮጵያ ጀርመን ግንኙነት ሰፊ መሆኑን ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ በዋናነት ቡና፣ አበባ፣ የጨርቃጨርቅ ውጤቶችን ወደ ጀርመን እንደምትልክ ገልጸዋል፡፡
ጀርመንም ማሽነሪዎችን፣ ለፋብሪካ ግብዓት የሚውሉ ኬሚካሎችን እና የኬሚካል ውጤቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ የዕዳ ሽግሽግና ማስተካከያ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውንም አንስተዋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ያጋጠመውን የውስጥ ግጭት ለመፍታት የተሄደባቸውን መንገዶች፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ፣ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እና ተግዳሮቶቹን ለመሻገር በመንግሥት በኩል ሁሉንም ኃይል አሟጦ ለመጠቀም እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ማስረዳታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ውይይትም፥ በተለይም የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ልትጫወተው የምትችለውን ሚና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አብራርተዋል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ የመሪዎቹ ውይይት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል የነበረውንና ያለውን በመቻቻል፣ በመግባባት እንዲሁም በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ያስቀጠለ ነው ማለት ይቻላል ብለዋል አምባሳደሩ በማብራሪያቸው፡፡
የውይይቱ መንፈስ በመከባበር፣ በመሠረታዊ ቁምነገሮች እና በሐሳቦች ዙሪያ መደረጉን ጠቅሰው፥ ከዚህ በፊት የጀርመን የቀድሞ መራሔ መንግሥቶች የተከተሏቸው የትብብር ግንኙነቶች እነዚህን የሚያንጸባርቁ ናቸው ብለዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!