የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲጀምር ተጠየቀ

By ዮሐንስ ደርበው

November 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን ድጋፍ ተደራሽ የማድረግ ሥራ በፍጥነት እንዲጀምር አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ጠየቁ፡፡

በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ካርል ሰኩ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች አቅርቦቱ እንዲጀመር ውሳኔ ማሳለፉን አድንቀዋል፡፡

አያይዘውም ድጋፉን ተደራሽ የማድረግ ሥራው በተቻለ ፍጥነት እንዲጀመር መጠየቃቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ድርጅቱ ለሚያደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ሕይወታቸውን በሚቀይሩ የልማት ፕሮጀክቶች በማሳተፍ በቋሚነት ማቋቋም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ከማስቀጠል አኳያ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!