አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጠረው የሰላም እጦት የኢንቨስትመንት ተቋማት ሥራቸውን ለማቋረጥ ተገድደው መቆየታቸውን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው÷ በክልሉ በተፈጠረው ችግር በኢንቨስትመንት ዘርፉ በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸውን ተናግረዋል፡፡
ሰላም በሌለበት ሁኔታ ኢንቨሰትመንት ሊታሰብ እንደማይችል ገልጸው÷ ኢንቨስትመንት ሰላምን በእጅጉ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት አዲስ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣና የነበሩትም ሥራ እንዲያቆሙ ምክንያት ሆኗል ያሉት አቶ ደሳለኝ÷ በተጨማሪም የተዘረፉና የወደሙ የኢንቨስትመንት ተቋማት መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ለመታደግና ወደ ሥራ ለማስገባት በተከናወነ ጥረት ሥራ ያቋረጡ የኢንቨስትመንት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም እንዲመጡ እየተሠራ ነው ሲሉ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
በሰላም እጦት ምክንያት ቆመው የነበሩ የልማት ፕሮጄክቶችም እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአማራ ክልል ለሁሉም የኢንቨስትመንት አማራጮች የተመቸ መሆኑን ጠቁመው÷ ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም በፍጥነት ወደ ሰላም መመለስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የሰላም ሁኔታውን በፍጥነት በማሻሻል ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ለማከናወን እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴውም መቆሙንም ጠቅሰዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!