የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ሀገራት ከደቡብ ኮሪያ በአይሲቲ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ልምድ መውሰድ አለባቸው – አምባሳደር ደሴ ዳልኬ

By Meseret Awoke

November 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት ከደቡብ ኮሪያ በአይሲቲ እና በቴክኖሎጂ በተለይም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገት ልምድ መውሰድ እንዳለባቸው በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡

አፍሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የልምድ ልውውጥ በማድረግ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በአምባሳደር ደሴ ዳልኬ የተመራ ልዑክ የዓለም አቀፍ ኮሪያ ሪፐብሊክ ፎረም 2023 በኮሪያ ሪፐብሊክ-አፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን አጋርነት ጉባኤ ላይ ተሳትፏል።

በጉባኤው ላይ አምባሳደር ደሴ እንዳሉት፥ ደቡብ ኮሪያ እና አፍሪካ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥ በማድረግ መስራት አለባቸው፡፡

የአፍሪካን እድገት የበለጠ ለማስቀጠል የዲጂታይዜሽን አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑንም አንስተው፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ከደቡብ ኮሪያ በአይሲቲ እና በቴክኖሎጂ በተለይም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገት ልምድ መውሰድ እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በአፍሪካ እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን የትብብር እድሎች ለማጉላት ደቡብ ኮሪያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን ምርጥ ተሞክሮዎች እንድታካፍል ጠይቀዋል።

የኮሪያ ሪፐብሊክ እና አፍሪካ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት አምባሳደር ዎን-ኪ ሊዮ በበኩላቸው፥ በኮሪያ ጦርነት ወቅት አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ድጋፍ ስታደርግ እንደነበርም ነው ያስታወሱት፡፡

በአፍሪካ እና በደቡብ ኮሪያ መካከልም ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በፎረሙ የደቡብ ኮሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት፣ በደቡብ ኮሪያ – የአፍሪካ አምባሳደሮች፣ የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ተመራማሪዎች መሳተፋቸውም ነው የተገለጸው።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!