የሀገር ውስጥ ዜና

በእነወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) የክስ ዝርዝር ላይ የሟቾችና የተጎጂዎች ዝርዝር ተካቶ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ታዘዘ

By ዮሐንስ ደርበው

November 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሽብር ወንጀል በተከሰሱት በእነወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) የክስ ዝርዝር ላይ የሟቾች እና የተጎጂዎች ስም ዝርዝር ተካቶ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ታዘዘ።

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ- ሽብርና ሕገ- መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

በፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ÷ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣ መስከረም አበራ፣ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ ሲሳይ አውግቾው ( ረ/ፕ)፣ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ መንበረ ዓለሙ እና ተስፋዬ መኩሪያን ጨምሮ 51 ግለሰቦች በአማራ ክልል ተከስቶ ከነበረው ሁከትና ግጭት ጋር በተያያዘ የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦ ነበር።

ከአጠቃላይ ተከሳሾቹ መካከል 24ቱ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ በጠበቆቻቸው አማካኝነት አጠቃላይ የክስ ዝርዝሩ እንዲሻሻል የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በኩልም ክሱ ሊሻሻል አይገባም የሚል መልስ መሰጠቱ ይታወቃል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን የክስ ይሻሻልልን ጥያቄና የዐቃቤ ሕግን መልስ መርምሯል።

በዚህም ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ የ217 ሟቾችን እና ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉ 297 ሰዎችን ስም ዝርዝራቸውን አካቶ እንዲያቀርብ ታዝዟል።

የንብረት ጉዳትን በተመለከተም ዓይነቱን፣ መቼና የት ጉዳት እንደደረሰ ጠቅሶ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ብይን ተሰጥቷል።

እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ክሶች ይሻሻልልን የሚሉትን የተከሳሾች መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል፡፡

ዐቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዲቀርብ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመጠባበቅም ለሕዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ