የሀገር ውስጥ ዜና

በድሬዳዋ የወባና የደንጊ ትኩሳት ወረርሽኝን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

By Feven Bishaw

November 23, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬደዋ አስተዳደር የተከሰተውን የደንጊ ትኩሳትና የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን የድሬዳዋ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ እንዳሉት÷ በትንኝ አማካኝነት የሚተላለፉት የወባና የደንጊ ትኩሳት በሽታዎች ዘንድሮ በተለየ መንገድ በወረርሽኝ መልክ ተከስተው የማህበረሰቡን ጤና እየጎዱ ነው።

በሽታዎቹን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ንፅህና ከመጠበቅ ጀምሮ ሕመም ሲሰማው ፈጥኖ ወደጤና ተቋማት በመሄድ እንዲታከም አስገንዝብዋል።

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በከንቲባ የሚመራ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸው፤ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ መረጃዎችን የማሰባሰብና የትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን የማጽዳት ሥራ በዘመቻ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የተሰጠውን የመከላከያ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ዝናብ ለትንኞች መራባትና ለበሽታው መስፋፋት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

በመሆኑም በሽታዎቹን ለመከላከል በትንኝ መራቢያ ሥፍራዎች ላይ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሽታዎቹን ከመከላከል ጎን ለጎን ለታመሙ ሰዎች አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ህሙማንን የመታደግ ሥራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዘንድሮ የተከሰተው የደንጊ ትኩሳት ወረርሽን የተለየና ያልተለመዱ ምልክቶች ከማሳየት ባለፈ ለሞት መንስኤም እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፤ ወረርሽኙን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያግዝ የጥናትና ምርምር ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም ዶ/ር ፅጌረዳ አመልክተዋል።

ወረርሽኙ ወደሌላ አካባቢ እንዳይዛመትም ከአጎራባች ክልሎችና ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል።