የሀገር ውስጥ ዜና

ለክልል አደረጃጀት የተሰጠው ምላሽ የሕዝብን ጥያቄ የመመለስ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው – አቶ አደም ፋራህ

By Shambel Mihret

November 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ለክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ እና የምስጋና መርሐ -ግብር ላይ የተገኙት አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፤ የክልሉ መመስረት ለህዝቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ለክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ ፓርቲው ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክትም ተናግረዋል።

ለዚህም የቀድሞውን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልን የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለመመለስ የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

ለህዝቦች የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነት፣ የአደረጃጀትና የመሳሰሉ ጥያቄዎች የህብረተሰቡን ዘላቂ ፍላጎትና ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ ምላሽ መስጠት ተገቢ እንደሆነም ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝቦች የተፈጠረላቸውን አደረጃጀት በመጠቀም ያላችውን እምቅ አቅም ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ ተግባር ላይ እንዲያዉሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው