አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክ/ከተማ አራት የመስግስት ይዞታዎች ላይ በተጭበረበረ መንገድ ካርታ አዘጋጅተው ቦታው እንዲወሰድ አድርገዋል የተባሉ 3 ተከሳሾች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ።
ተከሳሾቹ እንዲቀጡ ውሳኔ የሰጠው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ በህገወጥ መንገድ እንዲወሰድ አድርገዋል የተባለው ይዞታ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።
ተከሳሾቹ በግል ስራ ይተዳደራል የተባለው 1ኛ ተከሳሽ አማኑ ግዛው እንዲሁም የቡራዩ ክ/ከ የመሬት አስተዳደር የካርታ ዝግጅት ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ዳንዲ ቀና እና ሳኒ ግርማ ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ ባቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በቡራዩ ክ/ከ መሬት አስተዳደር የካርታ ዝግጅትና አረጋጋጭ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ በጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም በይዞታነት ያልተመዘገቡ አራት የተለያዩ ቦታዎችን በሀሰተኛ ሰነድ ተጠቅመው በቡራዩ መልካ ገፈርሳ በተባለ አካባቢ በሽር አህመድ በሚል ስም ካርታና የቦታ ፕላን በህገወጥ መንገድ አዘጋጅተው ለአንደኛ ተከሳሽ መስጠታቸው ተጠቅሶ በክሱ ላይ ተዘርዝሯል።
ይህንን በሀሰተኛ ሰነድ የተሰጠ ቦታን 1ኛ ተከሳሽ የኔ ነው በማለት ለሌሎች አካላት በሽያጭ ሲያስተላልፍ እንደነበርም በክሱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ በዚህ በተዘጋጀ ካርታና ፕላን በያንዳንዱ 200 ካሬ ሜትር ይዞታ ሆኖ የተሰጠ ሲሆን፣ የመንግስት ይዞታን በህገወጥ መንገድ በመውሰድ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን 4 ሚሊዮን 243 ሺህ 496 ብር ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል።
በአንደኛው ክስ ላይ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 3 በመተላለፍ የሚል ክስ ነው።
በሁለተኛ ክስ ላይ ደግሞ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ/ለ እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 /ሀ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነት በከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በዚህ የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ የቀረበው የሙስና ወንጀል ክስ ዝርዝር በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ሰባት የሰው ምስክሮችንና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቦ አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
ይሁንና ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት አንቀጽ እያንዳንዳቸው በሁለት አመት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
ተከሳሾቹ በህገወጥ መንገድ ካርታ በማዘጋጀት እንዲወሰድ አድርገዋል የተባለው አራቱም ይዞታ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።
በታሪክ አዱኛ