የሀገር ውስጥ ዜና

የካፒታል ገበያን ስኬታማ ለማድረግ የኦዲት ሥርዓቱ ዘመኑን የዋጀ ሊሆን ይገባል – እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

November 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኦዲት ትግበራ ባህል የተመለከተ የግምገማ መድረክ የኦዲት ድርጅት አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የሒሳብና ኦዲት አገልግሎት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

የካፒታል ገበያ ማቋቋምና የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በመፈቀዱ ከዚህ አኳያ ጥራት ያለው የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርት ወሳኝ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የኦዲት ባለሙያዎች ዘመኑ የደረሰበት ጥራት ያለው የኦዲት ተግባራትን ለማከናወን እንዲችሉ ጥራት ያለው የኦዲት ሥርዓት በመዘርጋት ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነት መረጋገጥ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የኦዲት ጉዳይ ሥነ-ምግባር ካልታከለበት ለብልሹ አሠራር የመዳረግ ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ በዚህ ረገድ የኦዲት ባለሙያዎች ሙያዊ መርህና ሞራልን ሊያስቀድሙ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኦዲት ዘርፉ ውጤታማ ሆኖ ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነት አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዲኖረው ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ÷ ታክስ የሚከፈለው እንዲሁም ባንኮች ብድር የሚሰጡት የኦዲተሮችን ሪፖርት መነሻ አድርገው በመሆኑ ዘርፉ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም ቦርዱ ኦዲተሮች አቅማቸውን እንዲገነቡ ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ በአግባቡ በማይሰሩት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑ አብራርተዋል።

በዚህም ሐሰተኛ ሪፖርት የሚያዘጋጁ፣ ፈቃድ ሳይኖራቸው ኦዲት የሚያደርጉ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የውጭ ኦዲተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳንኤል ጌታነህ÷ በመስኩ ሕግን ጠብቀው የሚሰሩ ኦዲተሮች እንዳሉ ሁሉ፤ የሐሰት ኦዲት ሪፖርት የሚያዘጋጁ ቀላል ቁጥር የላቸውም ብለዋል።