የሀገር ውስጥ ዜና

የኡስታዝ አቡበከር ሁሴንን መኪና ሊነጥቁ ነበር የተባሉ ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

By Feven Bishaw

November 24, 2023

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 14 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለን ግለሰብ በማገት ሊብሬውን በመቀየር መኪናውን ሊነጥቁ ነበር የተባሉ ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ።

ተከሳሾቹ የተከሰሱበት አንቀጽ ዋስትና የሚያስከለክል መሆኑን ተከትሎ ነው ዋስትናቸው ተነፍጎ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ የታዘዙት።

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ 1ኛ ተከሳሽ የሁለተኛ ተከሳሽ ወኪል የሆነው ፍፁም ተክሉ አፅብሀ፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የኡስታዝ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ ሆርዶፋ፣ በአዲስ አበባ አሸከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት ውስጥ የተሽከርካሪ አገልግሎት ባለሙያ ናቸው የተባሉት አብዮት አበራ፣ ልየው አሰፋ አንዱአለም፣ አለሙ ኦልጅራ እንዲሁም የአ/አ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቡድን ኃላፊ ዋና ሳጅን መኳንንት ተመስገን እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ቡድን አባል የሆነው ዋና ሳጅን ገመቹ ብርሃኑ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በአጠቃላይ በሰባት ተከሳሾች ላይ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህ በተመሰረተባቸው ክስ ላይ 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ወኪል በመሆን ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር የሆነውንና ከላይ የተጠቀሰውን ተሽከርካሪ አስቀድመው የተሽከርካሪውን መረጃ ለማግኘት ከ3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር “ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ” በሚል በግል ተበዳይ ስም ተመሳስሎ ከለሚ ኩራ ክ/ከ/ወ/10 የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ቅ/ፅ/ቤት እንደተሰጠ በማስመሰል በተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እና ያላገባ የምስክር ወረቀት መጠቀሙ በክሱ ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ በተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽህፈት ቤት ሙሴ መረሳ ኃይሉ ለሚባል ግለሰብ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን ነኝ በሚል ውክልና መሰጠቱን ዐቃቤ ህግ በክሱ ገልጿል።

በዚህ መልኩ በተሰጠ ውክልና ስልጣን መሰረት ደግሞ ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በእጃቸው በሌለ ተሽከርካሪ የሽያጭ ውል እንዲፈፀም ካደረጉ በኋላ በ5ኛ ተከሳሽ አማካኝነት በህገወጥ መልኩ ሊብሬ በማሰራት ንብረትነቱን ወደ 2ኛ ተከሳሽ እንዲዞር ማድረጋቸውም በክስ ዝርዝሩ ተመላክቷል።

ከዚህ በኋላ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም የግል ተበዳይ ኡስታዝ አበቡከር ተሽርካሪውን እያሽከረከረ ባለበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የድንገተኛ ስልክ ጥሪ ማዕከል 991 በመደወል መኪናው እንደተሰረቀበትና በመንገድ ላይ እየተነዳ እንዳየው በመግለፅ እንዲያዝለት ማመልከቱ ተጠቅሷል።

ነዚህም የፌዴራል ፖሊስ ኢንተለጀንስ ሰራተኛ ከሆነው 7ኛ ተከሳሽ ጋር በጋራ በመሆን መኪናውን አስቁመው እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ስራ በሚሰሩት የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በሆኑት አካላት አማካኝነት ተሽከርካሪው እንዲያዝ በማድረግ እና በሀሰት ተሽከርካሪው ከዚህ በፊት የጠፋባቸው መሆኑን በመግለፅ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ለቡ ፖሊስ ጣቢያ በማመልከት ተሕከርካሪውን ሊወስዱ ሲሉ የተያዙ መሆኑ በክሱ ተገልጿል።

3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጭ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር የግል ተበዳይን ተሽከርካሪ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም አስቀድሞ የዋጋ ግምት እንዲፃፍ በማድረግ እና ሽያጭ ተፈፅሟል በሚል ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ባለቤትነቱን ከግል ተበዳይ ከኡስታዝ አቡበከር ስም ወደ 2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲዞር ካደረገ በኋላ የግል ተበዳዩ በ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የተሽከርካሪ ቦሎ እድሳት ለማድረግ ወደ ተቋሙ በሄደበት ወቅት በህገወጥ የስም ዝውውር መደረጉንና ሀሰተኛ የተሽከርካሪው ሊብሬ በ2ኛ ተከሳሽ ስም እንዳለ እያወቀ ለግል ተበዳዩ ቦሎውን ያደሰለት መሆኑ በክሱ ተጠቅሶ ሰፍሯል።

በዚሁ መልኩ 4ኛ ተከሳሽ ደግሞ የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአዲስ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት የዳታ ኢንኮደር ባለሙያ በመሆን ሲሰራ በስራ ሰነድ ማጣራት እና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እያለበት ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነውን ተሽከርካሪ የባለቤትነት ስም መረጃውን ሳያጣራ እና ሳያረጋግጥ በሲስተም ላይ ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ወደ 2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲዞር ማድረጉን ዐቃቤ ህግ በክሱ አመላክቷል።

5ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአዲስ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት የተሽከርካሪ ፈቃድ አገልግሎት ባለሙያ በመሆን በማገልገል ላይ እያለ በስሙ ከንብረት ክፍል በወጣ ሊብሬ ሲስተም ላይ ሳይመዘገብ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነውን ተሽከርካሪ ባለቤትነት በ2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲሆን በማድረጉ ተጠቅሶ በክስ ዝርዝሩ ሰፍሯል።

6ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ተከሳሹ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ/ፖ/መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቲም ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ሳለ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር የሆነውን ተሽከርካሪ መረጃ በሚመለከት በህግ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጭ ምንም አይነት የወንጀል ጥቆማና አቤቱታ ባልቀረበበት እና የምርመራ ስራ ባልተጀመረበት ጉዳይ ላይ የተሽከርካሪው መረጃ እንዲላክለት ለአዲስ ከተማ ክ/ከ/መንገድ ትራንስፖርት ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ደብዳቤ በመፃፍ ማህደር ኮፒው እንዲመጣ በማድረግ ለ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች አሳልፎ የሰጠ መሆኑ ተመላክቷል።

በተጨማሪም በክሱ ላይ እንደሰፈረው 7ኛ ተከሳሽ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ሰራተኛ ሆኖ ሲያገለግል የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከተቋሙ ምንም አይነት የሥራ ስምሪት ሳይሰጠው የግል ተበዳይ ተሽከርካሪው ላይ እንዳለ በኮ/ቀ/ክ/ከ/ወ/01 ልዩ ቦታው ሳሚ ካፌ አካባቢ ሲደርስ በማስቆም እና ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ እንዲታሰር ማድረጉም ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ የሆነውንና የዋጋ ግምቱ 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቪ8 ተሽከርካሪ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ማህደሩን በመለወጥና በሽያጭ በማስተላለፍ ለመውሰድ ሲሉ የተያዙ መሆኑ ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ነበር የተከሰሱት።

ክሱ ለተከሳሾቹ ከደረሳቸው በኋላ ከተከሳሾቹ መካከል 5ኛ ተከሳሽ አለሙ ኦልጅራ ተሰውሮ ከነበረበት በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎ ዘግይቶ በችሎት ቀርቧል።

በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው የሙስና አዋጅ ድንጋጌ ዋስትና መብት የማያሰጥ መሆኑን ተከትሎም ተከሳሾቹ ዋስትና ተነፍገው ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዟል።

ዘግይቶ በቁጥጥር ስር የዋለው 5ኛ ተከሳሽም በተመሳሳይ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዟል።

በታሪክ አዱኛ