አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጋር ከዚህ ቀደም ሰጥቶ በነበረው ምክረ ሃሳብ አተገባበር ዙሪያ ውይይት ማድረጉን ገለጸ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከዕዙ ጋር ያደረገውን ውይይት በማስመልከት በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።
መርማሪ ቦርዱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፥ በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።
በዚህም በአማራ ክልል በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በሸዋሮቢት፣ በኮምቦልቻና ከክልሉ ውጪም በአዲስ አበባና በአዋሸ አርባ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመጎብኘት በወቅቱ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።
በጉብኝቱም የተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጡን በወቅቱ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በሲዳማ ክልል አፖስቶ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች አሉ የሚል ጥቆማ ደርሶት ቦታው ድረስ በመሄድ ባደረገው ማጣራት ምንም አይነት ተጠርጣሪ አለማግኘቱን መግለጹም የሚታወስ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ተዘዋውሮ በተመለከተውና ተጠርጣሪዎቹ ባነሷቸው ሃሳቦች ዙሪያ ከዕዙ ጋር ባደረገው ውይይት ምክረ ሀሳቦችን መስጠቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ በዛሬው ዕለት በሰጡት መገለጫ አንስተዋል።
በመግለጫቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ የተጠርጣሪዎችን አያያዝ በጎበኘበት ወቅት ወደ ማዕከል ያልተወሰዱ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን መመልከቱንና ይህንንም ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ገልጾ እንደነበር አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል የተጠርጣሪዎች የምርመራ ሂደት መፋጠን እንዳለበት ለዕዙ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን ጠቅሰው፥ ከዕዙ ጋር በተደረገ ውይይትም ተጠርጣሪዎች ወደ ማዕከል መሰብሰባቸው እንደተገለጸላቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጠርጥረው ከተያዙ 4 ሺህ 116 መካከል እስከ አሁን በሁለት ዙር 2 ሺህ 424 ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸው እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
ቀሪዎቹ 1 ሺህ 692 ተጠርጣሪዎች በሶስተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የሚቀላቀሉ መሆኑንና የተጠርጣሪዎች የምርመራ ሂደት እየተፋጠነ እንደሚገኝ ከዕዙ ጋር ባደረጉት ውይይት መረዳታቸውን አውስተዋል።
ቦርዱ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የተመለከተውን ጉዳይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባሻገር ለየኮማንድ ፖስቱ አመራሮች ምክረ ሃሳብ መስጠቱንም አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ረገድ ያለው አፈጻጸም መልካም መሆኑ በዕዙ በኩል መገለጹን ጠቅሰው ቦርዱ በቀጣይ በየአካባቢው ተዘዋውሮ ምልከታ በማድረግ መግለጫ እንደሚሰጥ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሌላ መልኩም የአማራ ክልል አሁናዊ የጸጥታ ሁኔታን አስመልክቶ ከዕዙ ጋር ባደረጉት ውይይት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መረዳታቸውን ነው የገለጹት።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በቀጣይ ጉብኝቱ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በማምራት የቀሩ ተጠርጣሪዎችን ሁኔታ የሚመለከት መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል።