የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ውይይት እየተካሄደ ነው

By Mikias Ayele

November 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ወቅታዊ ጉዳዮች የሚዳስስ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ውይይት በአራት ማዕከላት እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ውይይት ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት ባሕርዳርን ጨምሮ በአራት ማዕከላት እየተካሄደ ነው።

በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ገበያ ተስፋ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ አካባቢዎች በችግር ውስጥ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ዜጎች የእንቅስቃሴ መገደብ እና የልማት እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል እንደገጠማቸው በማመላከት፥ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ፅናት እና ቁርጠኝነት የተላበሰ መሪ እና የፀጥታ ሃይል መፍጠር እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

በሁሉም አካባቢዎች የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎችን በሚገባ መምራት፣ የኮሙኒኬሽን ግንኙነቱን የተስተካከለ ማድረግ እና የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

እየመጡ ያሉ ለውጦችን በሁሉም አካበቢዎች ወጥ እና ፅኑ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅቱን የሚመጥን የፖለቲካ ትንተና እንደሚጠበቅ በመጥቀስም ለሕዝብ ሰላም እና አንድነት አደጋ የሚሆኑትን መታገል እና ማስተካከል እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

የክልሉን ሰላም በሚገባ ማረጋገጥ እና ወደተሟላ ሰላም መሄድ ቀጣይ ሥራዎች ናቸው ያሉት ሃላፊዋ፥ ለዘላቂ ሰላም ከሕዝብ ጋር አንድነት በመፍጠር ውይይት ማድረግ የቀጣይ ሥራ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ክልሉን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደሲሆን፥ በመድረኩ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እና የምሥራቅ አማራ ዞኖችና ከተሞች መሪዎች ተገኝተዋል።

እንዲሁም በሦስተኛው ዙር ለመንግሥት መሪዎች ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና አጠናቅቀው ለተመለሱ የሰሜን ሸዋ ዞን፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርና የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር የወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች የቀጣይ ተግባራት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት በደብረ ብርሃን ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ ከስልጠና ቆይታ ለተመለሱ የመንግሥት አመራሮች የቀጣይ የሥራ አቅጣጫና የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በሦስተኛው ዙር ለመንግሥት አመራሮች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቅቀው ለተመለሱ የደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደብረታቦር እና ጎንደር ከተማ አስዳደሮችን ጨምሮ ሌሎች ዞኖች አመራሮች የቀጣይ ተግባራት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በግርማ ነሲቡ