የሀገር ውስጥ ዜና

አሁን ያለው የአየር ጸባይ ለእሳት አደጋ መከሰት አስተዋጾኦ የሚያደርግ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠየቀ

By Feven Bishaw

November 25, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምንገኝበት የአየር ጸባይ ለእሳት አደጋ መከሰትና መባባስ አስተዋጾኦ የሚያደርግ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ባለው የእሳት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡

አሁን ያለው ነፋሻማና ሞቃታማ የአየር ጸባይ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ላለው የእሳት አደጋ አስተዋጾ ያለው መሆኑንም ገልጿል።

ከዚህ አንጻርም ህብረተሰቡ እሳትና የኤሌክትሪክ ሀይል ምንጮችን በሚጠቀምበት ጊዜ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከኮሚሽኑ በተለያዩ አማራጮች የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲተገብር አሳስቧል።

ከዚህ አልፈው ለሚያጋጥሙ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያደረገ በመሆኑ አደጋ ባጋጠመ ጊዜ ህብረተሰቡ በ939 ወይም በ011-1-55-53-00 ፈጥኖ እንዲያሳውቅ ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡