አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ተቋማት ጥራትን የሥራቸው ማዕከል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ያዘጋጀው 10ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ማምሻውን በቤተ-መንግሥት ተካሂዷል።
በውደድሩ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 38 ተቋማት ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ÷ ተቋማት ጥራትን የሥራቸው ማዕከል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተቋማት ከተቀመጠ ደረጃ ጋር ውድድር በማድረግ የምርትና የአገልግሎታቸውን ጥራት ለማስጠበቅ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዛሬ ለሽልማት የበቁ ተቋማት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተቋማት በውድድር ሂደቱ ተሞክሮዎች፣ የሚሰጣቸውን ጠቃሚ አስተያየቶች የእቅዶቻቸው አካል በማድረግና ተቋማዊ አሰራሮችን በማስፋን ዘመን ተሻጋሪ መለያ ለመፍጠር መትጋት አለባችሁ ብለዋል።