የሀገር ውስጥ ዜና

ችግኞች እንዲጸድቁ በቅርበት መከታተልና መንከባከብ ያስፈልጋል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

By Shambel Mihret

November 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ በቅርበት መከታተልና መንከባከብ ያስፈልጋል ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን በሐዋሳ ከተማ ታቦር ተራራ ተገኝተው በክረምት የተተከሉ ችግኞችን የተመለከቱ ሲሆን÷ ችግኞችን ውሃ የማጠጣት ስነ-ስርዓትም አከናውነዋል፡፡

ሚኒስትሩ በወቅቱ÷ ለአረንጓዴ አሻራ የተጣለውን ግብ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት የተተከሉ ችግኞችን ጽድቀት በቅርበት መከታተልና መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡ የተከላቸውን ችግኞች የመንከባከብና ውሃ የማጠጣት ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስትሩ በሲዳማ ክልል በሚኖራቸው ቆይታ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ የተከናወኑና ሌሎች ልማቶችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።