አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ”ዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል ርዕስ 3ኛ ዙር ሥልጠና የወሰዱ የአማራ ክልል የጎንደር ቀጣና የመንግሥት አመራሮች በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሌሎች አካባቢ ተንቀሳቅሰው የወሰዱት ሥልጠና ለቀጣይ ሥራቸው ስንቅ እንደሚሆናቸው አንስተዋል።
በማሕበረሰቡ ዘንድ የሰላም እጦት፣ የመልካም አሥተዳደር ችግር እና የሥራ እድል ፈጠራ አለመኖር ተደጋግሞ ይነሳል፤ይህንን ባለድርሻ አካላት በአግባቡ በመሥራት መፍትሔ መስጠት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በም/ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል አሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ደሳለኝ ጣሰው÷በክልሉ የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
የነበረው የሰላም እጦት እየተሻሻለ መምጣቱን ያነሱት አቶ ደሳለኝ÷ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥም ከማኅበረሰቡ ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል።
በቀውስ ጊዜ የሚገጥሙ ችግሮችን ወደ ድል መቀየር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት መስጠታቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡
በአማራ ክልል ም/ርዕሰ መሥተዳድር ማእረግ የርዕሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው÷ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን መሥዋዕትነት እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡
ስለሆነም ለዘላቂና አስተማማኝ ሰላም አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት መክፈል ግድ ይላል ብለዋል።
ከተደቀነው ዘርፈ ብዙ ፈተና ለመውጣት ወጥ አቋም ያለው አመራር መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመው÷ በቆራጥነት የሚሠራና ሕዝብን የሚያገለግል ትክክለኛ አመራር ሰጪ ያስፈልጋል ነው ያሉት።