የሀገር ውስጥ ዜና

የመምህራንና የትምህርት አመራሮችን ዐቅም ለማጎልበት ገዢ መመሪያ የማሻሻል ሥራ መጀመሩ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

November 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመምህራን እና የትምህርት አመራሮችን ዐቅም ለማጎልበት የሚያስችል ገዢ መመሪያ የማሻሻል ሥራ መጀመሩን የትምህርት ሚኒስቴር አመለከተ።

ሚኒስቴሩ አዲሱን የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ተከትሎ ከ22 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የ2ኛ ደረጃ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት አሳትሞ ከ10 ሚሊየን በላይ ለክልሎች እና ለከተማ አሥተዳደሮች ማከፋፈሉንም ገልጿል።

ነገና ከነገ በስቲያ ለሚካሄደው 32ኛው የትምህርት ጉባዔ ቅድመ ምክክር በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን መድረኩ÷ በአጠቃላይ ትምህርት እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚል በሁለት ተከፍሎ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በመድረኩ ላይ÷ የራስ ገዝነት ዕድሎች እና ፈተናዎች የሚሉና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን÷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተሞክሮውን አጋርቷል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አየለች እሸቴ÷ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የመምህራን እና የትምህርት አመራሮችን ዐቅም ለማጎልበት የሚያስችል ገዢ መመሪያ የማሻሻል ሥራ ተጀምሯል ሲሉም ተናግረዋል።

የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡

በመራኦል ከድር

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!