የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የ2 ቅርሶችን ሕጋዊ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከዩኔስኮ ተረከበች

By Melaku Gedif

November 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ሕጋዊ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተረክባለች፡፡

በሳለፍነው መስከረም ወር በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ በተካሄደው 45ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ-ምድርን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለትም የቅርሶቹን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ኢትዮጵያ ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ማዕከል የአፍሪካ ቢሮ ሃላፊ ሙሃመድ ጁማ (ዶ/ር) መረከቧን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡