የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ግብርናን ማዕከል ያደረገ የኢንዱስትሪ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ለሰራችው ስራ ዩኒዶ እውቅና ሰጥቷታል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

By Feven Bishaw

November 28, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ግብርናን ማዕከል ያደረገ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ለሰራችው ስራ እና በሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) እውቅና ሰጥቷታል ሲሉ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ20ኛው የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኦስትሪያ ቪየና አቅንተው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይህን አስመልክቶና የኢትዮ-ኦስትሪያ ግንኙነትን በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ታዳጊ ሀገራት የመሰረተ ልማት አቅርቦትንና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት የፋይናንስ እጥረት፣ ታዳጊ ኢንዱስትሪን በማልማት በኩል የቴክኖሎጂ ና እውቀት ችግሮች አሉባቸው ያሉ ሲሆን÷ እነዚህ ችግሮች ያሉባቸው ሀገራት እጣ ፈንታቸው ግጭት የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሀገራቱ በርካታ የፖሊስ ማሻሻያዎች ሲያደረጉ መቆየታቸውንም ጠቅሰው፤ ጉባኤው በዋነኛነት እነዚህንና በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ቀደም ብለው የገቡትን ቃል በሚያከብሩበት እና ታዳጊ ሀገሮች ከችግሮቹ በሚላቀቁበት ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፖሊሲ ማሻሻያ ካደረጉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያም ተጠቃሽ ናት፤ የባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የስራ ዕድል አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሰረተ አማራጭ የኢነርጂ አቅርቦት ለማሻሻልና ግብርናን ማዕከል ያደረገ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ስራ ከሰሩት ተርታ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ለዚህም ዩኒዶ እውቅና ሰጥቷል ያሉት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዩ እንግድነት በመገኘት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ያቀረቡትም ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በመድረኩ የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ የተገኙ ለውጦችን ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ ማብራራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በፋይናንስ በቴክኖሎጂ እና በእውቀት ሽግግር እንደ ዩኒዶ ያሉ ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ላይ የተለጠጠ እቅድ አቅዳለች፤ ለዚህ መሳካት ፋይናስ፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ክህሎት ካላቸው ሀገራት ጋር ልምድ መውሰድ ያስፈልጋታል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከኦስትሪያው መራሄ መንግሥት ካርል ኔሃመር ጋር ከኦስትሪያ ልምድ ለመውሰድ፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እና የሀገሪቱ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሁኔታ መወያየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የህዝቦች ለህዝቦች ግንኙነት እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፤ የኦስትሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርጉ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታርግም ገልዋል፡፡

ካርል ኔሃመር÷ በኦስትሪያ በኩል በግብርና ልማት፣ በማዕድን በመሰረተ ልማት፣ በመንገድ ኔትወርክ እና በባቡር መንገድ ግንባታ ተባብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል ነው ብለዋል ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፡፡