አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 18 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጋራት ጥያቄ የምስራቅ አፍሪካን ቀጠናዊ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑት ላውረንስ ፍሪማን (ፕ/ር) ተናገሩ።
ላውረንስ ፍሪማን (ፕ/ር) ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጋራት ጥያቄ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን ወደ ግጭት ሳይሆን ወደ ጥሪት የሚያራምድ ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
እንደ ቀይ ባህር ያሉ የባህር መስመሮች ካላቸው የጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታ ባሻገር ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር እና ሁለንተናዊ የምጣኔ ሀብት እድገትን ለማሳለጥ ጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።
አያይዘውም በቀጣናው የሀገራት ልማትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በሮችን የመጠቀም ፍላጎትና መሻትም ተገቢነት ያለው ስለመሆኑም ነው የገለጹት።
ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕዝቦችን የኢኮኖሚ እድገት ለመጨመር አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ በመገንዘብ ለተፈፃሚነቱ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በቃለአብ ግርማ