የሀገር ውስጥ ዜና

ሙሉዓለም የባሕል ማዕከል በሕንድ የኢትዮጵያን ባሕልና ጥበብ እያሳየ ነው

By Melaku Gedif

November 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና አፍሪካን ወክሎ ከሳምንት በፊት ወደ ሕንድ ያቀናው ሙሉዓለም የባሕል ማዕከል በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወረ የኢትዮጵያን ባሕል እያሳየ ነው።

የኪነ ጥበብ ልዑኩን የመሩት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር)÷ ልዑኩ በከልካታ ከተማ የመድረክ ዝግጅቱን በተሳካ ሁኔታ ማቅረቡን ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት ምሽት ደግሞ በባንግሎር ግዛት ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ማቅረብ እንደጀመረ አንስተዋል፡፡

የባሕል ማዕከሉ በደረሰባቸው ከተሞች በሙሉ ኢትዮጵያን ወካይ ባሕላዊ ሙዚቃዎችን እና አለባበሶችን ወደ መድረክ ይዞ እየወጣ እያስተዋወቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በመድረኩ ላይ የተገኙ የውጭ ሀገር ታዳሚዎች ኢትዮጵያዊ የባሕል ሙዚቃዎችን እንዲያውቁ ብሎም የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም ለማስፋት ተሠርቷል ነው ያሉት ።

በ7ኛው የዓለም የባሕልና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ የሚሳተፈው ሙሉዓለም የባሕል ማዕከል ቡድን ባንግሎር ሶስተኛ መዳረሻው ከተማ ስትሆን በቀጣይም ወደ ሌላ የሕንድ ግዛት ተጉዞ ሥራዎቹን እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል፡፡