ጤና

በደብረ ብርሃን 30 ኪሎ ግራም እጢ ከአንዲት እናት በቀዶ ሕክምና ተወገደ

By Shambel Mihret

November 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 30 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ ከአንዲት እናት በቀዶ ሕክምና ማስወገዱን ገለጸ።

ታካሚዋ እናት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ምድር ነዋሪ ሲሆኑ፥ ለሁለት ዓመታት በሕመም የቆዩ እና በጤና ተቋማት ሕክምና ሲደረግላቸው እንደነበር ተገልጿል።

የሆስፒታሉ የማሕጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ዳግም ሽመላሽ÷ ዶክተሮችን ጨምሮ ስድስት የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች በቀዶ ሕክምናው መሳተፋቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሁለት ሰዓታትን የፈጀ የቀዶ ሕክምና በማድረግ እጢውን በተሳካ ሁኔታ ማስወገድ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ ከዚህ በፊት መሰል የቀዶ ሕክምና ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ዶክተር ዳግም÷ የአሁኑ ከዚህ በፊት ከነበረው በመጠን የሚለይ መሆኑን ተናግረዋል።

ታካሚዋ በአሁኑ ሰዓት በሙሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝም ተመላክቷል።

በሰላማዊት ሙሉነህ