የሀገር ውስጥ ዜና

ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 31 ግለሰቦች ላይ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

By Melaku Gedif

November 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 31 ግለሰቦች ላይ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቅዷል፡፡

የክስ መመስረቻ ጊዜውን ለዐቃቤ ሕግ የፈቀደው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት ነው።

ችሎቱ ከአንድ ሳምንት በፊት በስር ፍርድ ቤት ዋስትና የተፈቀደላቸው ተጠርጣሪዎችን መዝገብ በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ በተመለከተበት ተሰይሞ ይግባኙን ተመልክቷል።

በዚህ ቀጠሮ ወቅት መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን እንደጨረሰ እና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ እንዳስረከበ ገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ በይግባኝ አቤቱታ መዝገብ በመሰየም በሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት የክስ መመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ለደንበኞቻቸው በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደው የዋስትና መብት እንዲፀና ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ለዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቻ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

ከደላላና ጋር በመመሳጠር ከሕግ ውጪ በጉቦ ለውጭ ዜጎች ፓስፖርት በመስጠት እና ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ገምበታ እና ምክትል ዳይሬክተር ቴድሮስ ቦጋለን ጨምሮ አጠቃላይ በ31 ግለሰቦች ላይ ነው የክስ መመስረቻ ጊዜ የተፈቀደው። በታሪክ አዱኛ