አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ”የሐይማኖት ተቋማት አስተምህሮ ለሀገራዊ ምክክር ያለው ፋይዳና የሚዲያ አጠቃቀም” በሚል መሪ ሐሳብ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
በምክክር መድረኩ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ ሐጅ መስዑድ አደም÷ በኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እየሰራ ላለው ስራ ስኬታማነት የሐይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ሐይማኖቶች ስለሰላም ለምዕመኑ እያስተማሩ መሆኑን ጠቅሰው÷ የዛሬው መድረክ በቀጣይ በኮሚሽኑ ለሚሰሩ ሥራዎች ውጤታማነት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ የሀገራዊ ምክክሩ ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው መባሉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ የሀገራዊ ምክክር ተሳትፎ፣ በኮሚሽኑ የተከናወኑና ቀጣይ ሊከናወኑ በዕቅድ የተያዙ ተግባራትን በሚመለከትም ገለጻ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ የሐይማኖት ተቋማት አስተምህሮ ያላቸውን ፋይዳ አስመልክቶም ከክርስትና እና ከእስልምና ሐይማኖት አንፃር የሚዳስስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ተብሏል፡፡