የሀገር ውስጥ ዜና

ሴቶች በግጭት አፈታት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ሰላም ሚኒስቴር ገለጸ

By Shambel Mihret

November 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ሴቶች በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሩ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር “ፌምዋይስ ኢትዮጵያ” የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

“ፌምዋይስ ኢትዮጵያ” ሴቶች በግጭት መከላከልና አፈታት፣ በሰላም ግንባታ በሚደረጉ የድርድር ሂደቶች ላይ ሚናቸውን ከፍ ለማድረግ የሚሰራ ነው ተብሏል፡፡

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በወቅቱ÷ ሴቶች በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሚኒስቴሩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ከፍ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራትም መንግስት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ታየ ደንደአ በበኩላቸው÷ የሚካሄዱ የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት ሂደቶች ሴቶችን ያካተተ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ “ፌምዋይስ ኢትዮጵያ” በቀጣናዊ የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያለው አስተዋፅኦና ሴቶች በሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ ላይ ያላቸው ሚና በሚሉ ርዕሶች ላይ የፓናል ውይይት መካሄዱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡