የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የአይኤልኦ አባል የሆነችበትን 100ኛ ዓመት አስመልክቶ ጉባኤ ይካሄዳል

By Feven Bishaw

November 30, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) አባል የሆነችበትን 100ኛ ዓመት አስመልክቶ ከሕዳር 24 እስከ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ጉባኤ ይካሄዳል።

በሰራተኞች እና አሰሪዎች ዙሪያ የሚመክረው ጉባኤው ‘ማህበራዊ ምክክርን እና የጎለበተ ምርታማነትን በመጠቀም ማህበራዊ ፍትህን ማላቅ “በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ጉባኤው ያለፉት 100 አመታት ጉዞ የሚገመገምበት፣ ልምድ የሚወሰድበት፣ የወደፊት እቅዶች የሚተለሙበት እንዲሁም አዎንታዊ አስተዋጽኦ የነበራቸው አካላት ዕውቅና የሚሰጥበት እንደሚሆን ተጠቁሟል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ኢትዮጵያ የአይኤልኦ አባል በመሆን ቀዳሚ የአፍሪካ ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አይኤልኦ ለሰራተኞች ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን፣ በስራ ቦታ ላይ የሚደርስን ጥቃት ለመከላከል፣ ፍትህ እና እኩልነትን ለማስፈን አልሞ የተቋቋመ ሲሆን፤ ድርጅቱ ላለፉት 100 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር የሶስትዮሽ ግንኙነት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።

በትዕግስት አስማማው