አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት አቶ አብነት ገ/መስቀል የተከሰሱበትን የሙስና ወንጀል በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ አዘዘ።
ችሎቱ በአቶ አብነት ጠበቆች በኩል የክስ ዝርዝሩ እንዲሻሻል የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታሣሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቶ አብነት ገ/መስቀልን ጨምሮ በአጠቃላይ በአምስት ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም ዐቃቤ ሕግ አቅርቦት በነበረው ክስ ላይ እንዳመለከተው÷ አቶ አብነት ከሼክ አላሙዲን መሀመድ ጋር የጋራ ንብረታቸው የሆነውን በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 2 የሚገኘውን የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር ይዞታ ከሌሎች ተከሳሶች ጋር በመመሳጠር ቦታው ላይ ካርታ በማዘጋጀት ይዞታውን በ83 ሚሊየን ብር በመሸጥ ያለአግባብ መብት ተፈጥሮላቸዋል በሚል ነበር በሙስና ወንጀል ክስ ያቀረበው።
በዚህ ክስ የተካተቱ አራት ተከራሾች ግን በችሎት ያልቀረቡ ሲሆን፤ ክሱን በሚመለከት ከጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ እስረኛ ማቆያ በእስር ላይ የነበሩት አቶ አብነት የቀረበባቸውን የሙስና ወንጀል ክስ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዟል።
በሌላ በኩል አቶ አብነት ገ/መስቀል በ2015 ዓ.ም በ2ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በሌላኛው የቦሌ ታወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጅምር ግንባታ ያለበት 3 ሺህ 383 ካሬ ሜትር ይዞታን ያለአግባብ ባለመብት በመሆን ይዞታው ላይ ካርታ በማውጣት ከ321 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሸጥ አድርገዋል ተብለው ነበር፡፡
በዚህም ከሌሎች ከመሬት አስተዳደር ሰራተኞች ጋር ቀርበውባቸው ከነበሩ 3 ክሶች መካከል ሁለቱ ክሶች በችሎቱ ዳኛ ከአንድ ሳምንት በፊት እንዲቋረጡ መደረጉ ይታወቃል፡፡
በታሪክ አዱኛ