የሀገር ውስጥ ዜና

የበርበሬ ምርት በስፋት ለገበያ እየቀረበ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ

By Melaku Gedif

December 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበርበሬ ምርት በስፋት ለገበያ እየቀረበ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የቡና እና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ተፈራ ዘርፉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኢትዮጵያ ከፍተኛ የበርበሬ ምርት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ቀዳሚው ነው፡፡

የበርበሬ ምርት በክልሉ በሚገኙ የስልጤ፣ ጉራጌ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ሃላባና የም ዞኖች እንዲሁም የተለያዩ ልዩ ወረዳዎች በስፋት እንደሚመረት አንስተዋል፡፡

በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን 27 ሺህ 733 ሔክታር መሬት በበርበሬ መልማቱን ጠቁመው÷ ከዚህም 300 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

አሁን ላይም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የበርበሬ ምርት በስፋት ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምርቱ ነጋዴዎች፣ ዩኒየኖች እና የባልትና ዘርፍ ነጋዴዎች ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ ነው ለገበያ እየቀረበ የሚገኘው፡፡

የገበያ ትስስሩን በመላ ሀገሪቱ ለማሳለጥ እና ጥራቱን የጠበቀ በርበሬ ለገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተለይም በተጠቃሚው ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው የማረቆ ፋና በርበሬ ዝርያ ላይ እሴት ጨምሮ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ