የሀገር ውስጥ ዜና

ቻይና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

By Feven Bishaw

December 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በቻይና የብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና ገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ከቻይና ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ጊዜ የሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ቻይና በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ትምህርትና ጤናን ጨምሮ በሁሉም መስክ የምታደርጋቸው ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነስቷል።

ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ በወቅቱ እንዳሉት፤ ቻይና የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር በመሆን በሁሉም መስኮች የምታሳየው ትብብር የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ የልማት አጋርነት የበለጠ ያሳድጋል።

ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአረንጓዴ ልማት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን አብራርተው፤ የግብርና ሜካናይዜሽን ዘዴን በመጠቀም ግብርናውን በማዘመንና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ቻይና ልምዷን ለኢትዮጵያ እንድታጋራ ጠይቀዋል።

የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብና የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ማመቻቸት እንደሚገባም አመልክተዋል።

በቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዱ ጂሃኦ በበኩላቸው ሀገራቸው ግብርናውን በማዘመን ምርትና ማርታማነትን ለማሳደግ የወሰደቻቸውን እርምጃዎች አብራርተዋል።

ቻይና በክላስተር በማረስና የግብርና መካናይዜሽንን በመጠቀም ምርቶችን በብዛትና በጥራት እያመረተች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት ወዲህ የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ለማሳደግ እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ጥበቃ ላይ እያሳየችው ያለው ተሳትፎ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቻይና የኢትዮጵያን ግብርናን ለማዘመን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን የምታደርግ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።

የሁለቱን ሀገራት የፓርላማ ለፓርለማ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ የልማት አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት ወደ ቻይና ሄደው የግብርናውን ዘርፍ እንዲጎበኙ ዕድል ይመቻቻል ብለዋል።