የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በጂዛን የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተሳተፉ

By Mikias Ayele

December 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሳዑዲ ጂዛን በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በፎረሙ አምባሳደር ሌንጮ ÷በኢትዮጵያ በሚገኙ ሰፊና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ በቱሪስት መስሕቦች እንዲሁም በመንግሥት ምቹ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ለውጦች ላይ ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደሩ ከፎረሙ ጎን ለጎንም የጂዛን ከተማ አስተዳዳሪ ከሆኑት ልዑል መሐሙድ ቢን ናስር ቢን አብድላዚዝ አል ሳዑድ እና ምክትላቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚኖረው የኢኮኖሚ ትብብር እና በወደብ ተጠቃሚነት ዙሪያ መክረዋል።

በተጨማሪም ከጂዛን ከተማ የንግድ ቻምበር ምክትል ፕሬዚዳንት እና ከተለያዩ የሳዑዲ ባለሃብቶች ጋር በግብርና፣ በማዕድንና  አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሌንጮ የሳዑዲ ዓረቢያ የቢዝነስ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውንም የውጭ ጉዳ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡