አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት የሚሳተፉ ተወካዮችን ማስመረጥ ጀምሯል፡፡
ሒደቱ በተለያዩ ምዕራፎች የሚከናወን ሲሆን ÷ ዛሬ በመጀመሪያው ዙር ከዞን አንድ ከሰመራና ሎጊያ ወረዳዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ተደርጓል፡፡
ተሳታፊዎች ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ይወክሉናል የሚሏቸውን ሁለት ሁለት ግለሰቦች ከአንድ ተጠባባቂ ጋር በየወረዳቸው እና በየማህበረሰብ ክፍሎቻቸው ነው የመረጡት ፡፡
በቀጣይ በዞን አንድ ውስጥ ካሉ ሌሎች አስር ወረዳዎች ተወካዮችን የማስመረጡ ሂደት እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ ከ50 በላይ ከሚሆኑ ወረዳዎች የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ3 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተገለጸው፡፡
በሒደቱም ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል አስር አስር ሰዎች የሒደቱ ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በቀጣዮቹ ቀናትም ኮሚሽኑ የሚያስተባብረው የተወካዮች መረጣ በዱብቲ፣ አሳይታ፣ ጭፍራ፣ አዳአር፣ ሚሌ፣ ኢሊዳር እና ኮሪ ከተሞች እንደሚቀጠል ተገልጿል፡፡