አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመንግሥት አመራር አባላት እየተሰጠ ያለውን ስልጠና እየተከታተሉ ያሉ ሰልጣኞች ስልጠናው አንድነቷ የተጠበቀና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት ዐቅም መፍጠሩን ገለጹ፡፡
በባሕር ዳር የስልጠና ማዕከል “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተሰጠ የሚገኘው 4ኛ ዙር የመንግሥት አመራር አባላት ስልጠና ቀጥሏል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደገለጹትም÷ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ችግር ለመውጣት የአመራሩ ዐቅም ግንባታ ስልጠና ለውጥ የሚያመጣ ነው።
ገዥና የወል ትርክቶች ላይ አተኩሮ በመሥራት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጉዞ ማሻገር የሚያስችል ዐቅም መፍጠሩንም ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን አጠናክሮ በማስቀጠል በኅብረ-ብሄራዊ አንድነት ኢትዮጵያን ለመገንባት የስልጠናው ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አመራሮች ልምድና ተሞክሮ ለመቀያየር እድል የሰጠ በስለሆነ በቀጣይ መጠናከር እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
የመንግሥትን አሠራር በቴክኖሎጅ በማስደገፍ ሙስናን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ብሎም ለሕዝቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ስልጠናው ዐቅም ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡