የሀገር ውስጥ ዜና

ልዩነቶችን ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

By Mikias Ayele

December 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የደቡብ ወሎዞን አሥተዳደር ጠየቀ፡፡

“ለዘላቂ ሠላም ግንባታ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ በደቡብ ወሎ የደሴ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ እንደገለጹት ÷ ጽንፈኛ ኃይሉ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት የፌደራልና የክልሉን መንግሥት እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ሥም ማጥፋት ላይ ተጠምዷል፡፡

ሕዝቡም ይህን የተሳሳተ መረጃ እንዲያወግዝ እና ላላወቁትም እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል፡፡

ልዩነቶችን በውይይት መፍታትና ዘላቂ ሠላም የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን በበኩላቸው ÷ የአማራ ክልል ሕዝብ ሠላም አግኝቶ በማኀበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተሳትፎ በማድረግ ሠርቶ መለወጥና ማደግ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡

ለዚህም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

በመድረኩ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡