የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የበጋ የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር አስጀመሩ

By Feven Bishaw

December 03, 2023

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የበጋ የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር አስጀመሩ።

በመርሐ ግብሩ ላይ 3 ሺህ 200 ቤቶችን ያስገነቡ ሲሆን፥ ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችንም አስጀምረዋል።

በከተማዋ በክረምት የበጎ ፈቃድ ስራ ከ1 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

በዚህም የአቅመ ደካሞችና የሃገር ባለውለታ ወገኖች 3 ሺህ 500 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን፥ ከግማሽ ሚሊየን ለሚልቁ ወገኖችም ማዕድ መጋራቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የህዝቡን የኑሮ ጫና የሚያቀሉ ፕሮጀክቶችን የመንደፍ እና የትውልድ ግንባታ ስራዎችን ውጤታማነት የሚያሳድጉ ሌሎች ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቅሰዋል።

ከንቲባዋ ይህን ራዕይ በመጋራት ለተሳተፉ ልበ-ቀና ባለሃብቶች ምስጋና በማቅረብ፥ ሌሎች ባለሃብቶችና ነዋሪዎች በዚህ ስራ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።