የሀገር ውስጥ ዜና

ስልጠና ላይ የሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት የልማት ስራዎችን ጎበኙ

By Feven Bishaw

December 03, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ”ዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ማዕከላት 4ኛ ዙር ስልጠና እየተከታተሉ የሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የዲላ ማዕከል ሰልጣኞች በጌዴኦ ዞን የግብርና ልማት ስራዎች፣ የማር ምርትና የቡና ኢንዱስትሪ የስራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።

በዩኔስኮ የተመዘገበውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር አካል የሆኑ የትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ ስፍራዎችንም ጎብኝተዋል።

በተመሳሳይ የጂንካ ማዕከል ሰልጣኞች የኣሪ ዞን የልማት ስራዎችን፣ የጂንካ ማረሚያ ተቋምን፣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክትን፣ ኢንተርፕራይዞችንና፣ ጂንካ ዩኒቨርሲቲን ተመልክተዋል።

የወላይታ ሶዶ ማዕከል ሰልጣኞችም እንዲሁ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች እየተከናወኑ የሚገኙና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የመንግስት አመራር አካላቱ በወላይታ ሶዶ ከተማ የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴንም መመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ የሐዋሳ ማዕከል ሰልጣኞች በሲዳማ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።

አመራሮቹ ከተመለከቷቸው የልማት ስራዎች መካከል በሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም ሸበዲኖና ሌሎች ወረዳዎች እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ይገኙበታል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ተግባራዊ ሆነው በርካታ የክልሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የእንስሳት ሀብት ልማት ስራዎች እንዲሁም የሳሙናና የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችም የጉብኝቱ አካል ናቸው።

የአምቦ ስልጠና ማዕከል ስልጣኞችም የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን የመስክ ምልከታዉ ሠልጣኞች ከንድፈ ሀሳብ ባሻገር ከተግባር ተሞክሮና ከልምድ መማማር የሚያስችል እና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠናከር እድል የፈጠረላቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በጅግጅጋ ማዕከል ሰልጣኞችም ጅግጅጋ ከተማና አካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ የጅግጅጋ ዘመናዊ ችግኝ ጣቢያን፣ ሻሂድ የመኪና መገጣጠሚያ ድርጅትን፣ ሆፕ የዳቦ፣ ማካሮኒና የዱቄት ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴን እንዲሁም በፋፈን ከተማ የሚገኘውን ዘመናዊ የግመል እርባታ ማዕከልን እና የመሠረተ ልማት ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡