አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች አካታች አገልግሎትን መስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር!’ በሚል መሪ ሀሳብ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም ለ32ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተከብሯል።
ቀኑን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ባለድርሻና አጋር አካላት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
አካል ጉዳተኞች ኑሯቸው እንዲሻሻል ተቀናጅቶ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለለዚህ የሚረዳ አስገዳጅ ህግ እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ተቋማትም ለአካል ጉዳተኞች አካታች አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው አብዲሳ በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁላችንም ሀላፊነት ነው ብለዋል።
የተጀመሩ አበረታች ስራዎች በቀጣይም ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰራባቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።