የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን ለማስፋፋት የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ትፈልጋለች

By Feven Bishaw

December 04, 2023

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን ለማስፋፋት የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንደምትሻ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በዱባይ እየተካሄድ በሚገኘው የኮፕ-28 ጉባኤ የፓናል ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ልምድ አጋርተዋል።

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት እርምጃዎችን ከሀገራዊ ልማቱና ከግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ጋር በማጣጣም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን እውን ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ በመረጃ የዳበረ እና ዘላቂ የሆነ የከተማ ፕላን አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

“የታዳሽ ኃይልን በማጠናከር፣ ስማርት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ፣ የሀይል አጠቃቀምን በማመጣጠንና ስነ ምህዳርን በመጠበቅ እንዲሁም የካርበን ልቀትን በመቀነስ የልማት ሽግግሩን እውን ለማድረግ ሀገራዊ ራዕይ አለን” ሲሉም ገልጸዋል።

የግሉ ዘርፍ አካላት የአየር ንብረትን ታሳቢ ያደረገ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ መንግስት በአቅም ግንባታና በልምድ ልውውጥ ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

መንግስት ለስራ ፈጠራ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታታ መዋቅራዊ ሪፎርም እየተገበረ መሆኑም በመድረኩ ተነስቷል።