የሀገር ውስጥ ዜና

የ12ኛ ክፍል ፈተና መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ፈተና ወደሚታረምበት አዳራሽ ሊገባ ነበር የተባለው ተከሳሽ ያቀረበው መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

By Feven Bishaw

December 04, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ፈተና ወደሚታረምበት አዳራሽ ሊገባ ነበር የተባለው ተከሳሽ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ውድቅ ተደረገ።

ችሎቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የክስ መቃወሚያው ውድቅ የተደረገበት ተከሳሽ ይድነቃቸው ተኮላ ይኼይስ፤ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ 2 ስር የተመለከተዉን ድንጋጌ ተላልፏል በሚል በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበበት መሆኑ ይታወሳል።

በቀረበው ክስ ላይ ተከሳሹ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው የስራ ማስታወቂያ ተመዝግቦ በፈተና አመቻችነትና ለእርማት ስራ በጊዜያዊነት መቀጠሩ ተጠቅሷል።

በተለይም ከነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ነሀሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ውስጥ የተቀመጡና ለእርማት የተዘጋጁ የ18 ተማሪዎች የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መልስ መስጫ ወረቀቶችን ይዞ መውጣቱ በክሱ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል።

ከዚህም በኋላ በነሀሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 አካባቢ በፈተና ወቅት የተፈታኝ ተማሪዎች የመልስ መስጫ ወረቀቶች ያልሆኑና የፈተና መልስ ተቀልሞባቸው (ተሞልቶባቸው) የተዘጋጁ 33 የመልስ መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ፈተና ወደሚታረምበት አዳራሽ ሊገባ ሲል በተደረገ ቁጥጥር በፍተሻ የተያዘ በመሆኑ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተገልጿል።

በተጨማሪም በተከሳሹ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 44 የ2015 ዓ.ም ተፈታኝ ተማሪዎች የመልስ መስጫ ወረቀቶችና 10 ደግሞ ተመሳስለው የተዘጋጁ ሀሰተኛ የመልስ መስጫ ወረቀቶች የተገኙ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ ተከሳሹ ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሶ ክሱ በተረኛ ችሎት እንዲደርሰው ከተደረገና ክሱ በችሎት ከተነበበ በኋላ ክስ እንዲሻሻልለት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርቦ ነበር

በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በኩል ደግሞ ክሱ ግልጽ መሆኑ ተጠቅሶ ሊሻሻል አይገባም የሚል መልስ ተሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ክሱ እንዲሻሻል የቀረበው ጥያቄ ህጋዊ መሰረት የለውም በማለት ውድቅ አድርጓታል።

ተከሳሹም በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹ እንዲሰሙለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግን ምስክሮች ለመጠባበቅ ለህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ