የሀገር ውስጥ ዜና

የዕዙ አመራሮች ከምሥራቅ ጉጂና ምሥራቅ ቦረና ዞኖች የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ተወያዩ

By ዮሐንስ ደርበው

December 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ዕዝ ከፍተኛ አመራሮች ከምሥራቅ ጉጂ እና ከምሥራቅ ቦረና ዞኖች አመራሮች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

የዞኖቹን ሰላምና ደኅንነት ሲያውኩ እና የሕዝቡን መደበኛ ሕይወት ሲያናጉ በነበሩ ሕገ-ወጥ ታጣቂዎች ላይ በሰራዊቱና በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጀኔራል አድማሱ ዓለሙ ተናግረዋል፡፡

በዞኖቹ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎችም መደምሰሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችም በኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እጃቸውን እየሰጡ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

የምሥራቅ ቦረና ዞን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሃመድ ኑራ አሬሮ በበኩላቸው÷ በጠላት ተይዘው የነበሩ ቀበሌዎች በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃ ነፃ መውጣታቸውንና መደበኛ የመንግሥት መዋቅር ሥራ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡

በሰላም እጦት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የመሰረተ ልማት እና የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች ሥራ መጀመራቸውንም አስረድተዋል፡፡

ሕዝቡ ከሰራዊቱ ጋር ያለው መልካም ግንኙነት ከምንጊዜውም በበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱን እና ጠላት የሚንቀሳቀስባቸውን አካባቢዎች ለሰራዊቱ በማጋለጥ ኃላፊነታነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!