የሀገር ውስጥ ዜና

የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት እንደሚገባ ተገለጸ

By Shambel Mihret

December 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዜጎች የምትመች ሀገር ለመፍጠርና የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የደቡብ ኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ቢሮ ያዘጋጀው ዓለም አቀፉ የበጎ ፈቃደኞች ቀን “የእያንዳንዱ ሰው የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ድምር ውጤት ሃያልነት” በሚል መሪ ሃሳብበአዲስ አበባ ተከብሯል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በመርሐ ግብሩ÷ ምቹ ሀገር ለመፍጠርና የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ ስራ ዓለም አቀፋዊ ትብብር በመፍጠር ዓለምን ለሰው ልጆች የምትመች ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ሁሉም ሰው በእውቀቱ፣ በሙያውና በገንዘቡ የሚችለውን ያክል የበጎ ፈቃድ ስራ ቢሰራ የማይፈታ የማህበረሰብ ችግር እንደማይኖር ማመልከታቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዲዮግ ቾ÷ ቀኑ በጎ fቃደኞች ለማህበረሰብ ለውጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅናና ምስጋና ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡