አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በምርምር ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍና ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢትዮጰያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ገለጹ።
የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት 10ኛ የምስረታ በዓሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አክብራል።
አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ÷ ቻይና የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረገች ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመው ÷ ሀገራቸው በተለይም በልማት፣ በትምህርት፣ ስልጠና እና የምርምር ዘርፎች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል በዚህ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም የጎላ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ በዩኒቨርሲቲው ለ10 ዓመታት የቆየው የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት የሁለቱን ሀገራት ቋንቋ፣ ባህልና መልካም ተሞክሮ ለመለዋወጥ በር የከፈተ ነው ብለዋል።
የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲና የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቻይና ኤምባሲ በኩል ቀደም ሲል በጋራ ለመሥራት የፈረሙትን ስምምነት ለቀጣዮች አምስት ዓመታት ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!