የሀገር ውስጥ ዜና

ኮማንድ ፖስቱ ከቡሬ ከተማና አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ተወያየ

By ዮሐንስ ደርበው

December 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራብ ጎጃም ኮማንድ ፖስት ከቡሬ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

ውይይቱንም÷ የኮሩ አዛዥ እና የምዕራብ ጎጃም ኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል መለስ መንግስቴ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ እና የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ምስጋናው ጌትነት መርተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ አመራሮቹ አካባቢው ምርታማ በመሆኑ ልማትና ዕድገት እንጂ ሁከትና ብጥብጥ እንደማይመጥነው አስገንዝበዋል፡፡

አሁን የተፈጠረውን ሰላም ለማደፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎችን ሕብረተሰቡ በቃ ሊላቸው እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

የዞኑን ሠላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ፣ የተቋረጠው ትምህርትና የልማት እንቅስቃሴም እንዲቀጥል ነዋሪው ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ ለሕዝቡ የሚከፍለው ዋጋ የሚለካው በሕዝቡ ሰላም እና ኑሮ መሻሻል በመሆኑ÷ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እንደሚሠራ አመራሮቹ አረጋግጠዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም÷ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የሰላም መደፍረስና ግጭት በመከላከያ ሠራዊቱ መስዋዕትነት ተቀልብሶ አካባቢው ተኩስ የማይሰማበትና የተረጋጋ ቀጣና ሆኗል ብለዋል፡፡

የንግድ ቦታዎች እንዲከፈቱ፣ የመሥተዳድር አካላትና ድርጅቶች አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም የተቋረጠው የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀመር በመወሰኑ የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!