አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃ መገኛ አካላትን በዘላቂነት ለመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ወሳኝ ነው ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ በ28ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ባዘጋጀውና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ላይ በተመከረበት መድረክ ላይ ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በዚህም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥመውን ከንፁህ መጠጥ ዉሃ ጋር የተገናኙ ችግሮች መቀነስ እንዲቻል ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይ የዉሃ መገኛ አካላትን በዘላቂነት ለመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንዲሁም በመንግስትና በተለያዩ የልማት አጋሮች ድጋፍ እየተተገበሩ የሚገኙትን አየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የመጠጥ ውሃ ፕሮግራም እና የግድቤን በደጄ ፕሮጀክትን እንደ ማሳያ አንስተው አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ እስካሁን እያደረገ ካለው አስተዋጽኦ ላቅ ባለ መልኩ የልማቱ አጋዥ ሆኖ እንዲቀጥልና በጉባዔው እና ሌሎች ተመሳሳይ አለም አቀፍ መድረኮች ዉሃ የሁሉም አጀንዳዎች መጀመሪያ መሆኑን መረጋገጥ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።