አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአመራሩን አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያን ማፅናት ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በጎንደር የስልጠና ማዕከል አራተኛ ዙር ለተሳተፉ መካከለኛ አመራሮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም አሁናዊ ችግሮችን በጋራ ለመሻገር የአመራሩ ቁርጠኝነት በተግባር የተገለፀ መሆን አለበት ብለዋል።
አመራሩ በስልጠና ያገኘውን እውቀትና ክህሎት በየአካባቢው ህዝቡ ለሚያነሳቸው ችግሮች መፍቻ መንገድ አድርጎ መጠቀም ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡
የአራተኛው ዙር ስልጠና በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላትም ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች ለጎንደር ፋሲል አብያተ መንግስት ጥገና የሚውል ከ600 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ስጦታ አበርክተዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩ አቡሃይ በበኩላቸው÷ለ13 ቀናት ሲሰጥ የነበረው የመካከለኛ አመራር ስልጠና በርካታ ልምዶችን አመራሩ ያገኘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምናለ አየነው