አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ጉባዔ እየተሳተፉ የሚገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከሞሮኮ ኢነርጂ እና ዘላቂ ልማት ሚኒስትር ሌኢላ ቤናሊ(ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል::
ሚኒስትሮቹ በታዳሽ ሀይል ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ነው የልምድ ልውውጥና ውይይት ያካሄዱት፡፡
ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን አንስተው፤ የሞሮኮ መንግስት ለኢትዮጵያ ውሃና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እያደረገ ላለው የአቅም ግንባታ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
እንዲሁም የሞሮኮ ባለሀብቶች በታዳሽ ኢነርጂ ላይ ያላቸውን ልምድ ለኢትዮጵያ እንዲያካፍሉ እና በዘርፉ መዋዕለነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡