አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ የኮሮና መከላከያ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገውን የኳታር መንግስት አመሰገኑ።
የኳታር መንግስት በኳታር የልማት ፈንድ አማካኝነት ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶችን በዛሬው እለት ለኢትዮጵያ ድጋፍ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፥ “የኳታር መንግሥት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች፣ የሕክምና ጓንቶች፣ ፊትን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍኑ እና ሰውነትን ከንክኪ የሚከላከሉ ልብሶች እንዲሁም ሌሎች ኮቪድ19ን የመከላከያ ግብአቶች ስለላከልን አመሰግናለሁ” ብለዋል።
“ወረርሽኙን ለመግታት የምናደርገውን ጥረት ስለደገፋችሁ አድናቆቴ የላቀ ነው” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኳታር መንግሥት በኢትዮጵያ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ያበረከተውን የቁሳቁስ ድጋፍ በዛሬው እለት አስረክቧል።
የኢፌዲሪ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ድጋፉን ተቀብለዋል።
ድጋፉም 8 ሺህ 500 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው የሕክምና ቁሳቁስ ሲሆን፥ የፊት ጭምብሎች፣ ጋዎን፣ የፊት መከላከያ(ሺልድ)፣ የእጅ ጓንትና ሌሎችም ለኮሮናቫይረስ መከላከያነት የሚውሉ ናቸው።
በዚሁ መሠረት 470 ሺህ ማስክ፣ 70 ሺህ ኤን 95 የፊት ጭምብል፣ 60 ሺህ ጓንት፣ 12 ሺህ 500 የፊት መከላከያና 5 ሺህ 700 የሕክምና ባለሙያዎች ሙሉ የሰውነት መሸፈኛ ቁሶች ናቸው።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።