የሀገር ውስጥ ዜና

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር የፌዴራል ሥርዓትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ

By ዮሐንስ ደርበው

December 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓትንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በማስመልከት በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ ሲምፖዚዬም ላይ አፈ ጉባዔው ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህላቸውና ማንነታቸው ተከብሮ በአንድነት የሚኖሩባት ሕብረ ብሔራዊት ሀገር ናት ብለዋል።

በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ አሰባሳቢ እና ብሔራዊነት ትርክት መገንባት በሚያስችል መልኩ እየተከበረ መሆኑን አንስተዋል።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ባህል፣ ማንነት፣ እሴትና ወግ ሌሎች እንዲያሳዩ ያስችላልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ልዩነታቸው ተከብሮ የጋራ እና የወል ባህላቸውና ማንነታቸውን እንዲጋሩ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሕብረ ብሔራዊትና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ እና በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለዚህም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘላቂ ሰላም መከበርና ለሀገራዊ አንድነት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌዴራሊዝም አንኳር ፍልስፍና አብሮነት በመተማመን መንፈስ ሥርዓት መገንባት መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ በተገመደው ሕብረ ብሔራዊነታችን ውስጥ ያለውን ውበት ለዓለም የምናሳይበት መድረክ ነው ብለዋል።

በመላኩ ገድፍ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!