አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከ8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰብዓዊ ድጋፍ ሊያሰራጭ መሆኑን ገልጿል፡፡
መንግስት ለሶስተኛ ዙር የቅድሚያ ቅድሚያ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታውን ለማሰራጨት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ነው ያመላከተው።
በአጋር አካላት ይቀርብ የነበረው ዕርዳታ በጊዜያዊነት መቋረጡን ተከትሎ መንግስት ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ ወገኖች በሁለት ተከታታይ ዙሮች የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
ይህም 7 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም እስከ ሕዳር ወር 2016 ዓ.ም ተደራሽ ማድረጉን አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለሦስተኛ ዙር በቅርቡ ወደ ሥራ የተመለሱትን አጋር ድርጅቶች ጭምር በማስተባበር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ድጋፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ፍላጎት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ድጋፍ ለሚፈልጉ የተፈናቀሉ ዜጎችና በድርቅ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ወገኖች የሚደረግ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡
በዚህም ከ86 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ ዕርዳታ በዓይነት እና ከብር 560 ሚሊየን በላይ ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ በታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም ለማሰራጨት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ዕርዳታ የማጓጓዙ ሥራም ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር ሲሆን አጠቃላይ ድጋፉም በገንዘብ ሲሰላ ከ8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ይሆናል መባሉንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡
በቅርቡ በድርቅ አደጋ የተጠቁ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡