አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሁሉም አውዶች አሸናፊ እንድትሆን አንድነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመለከተ።
18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መልዕክት አስተላልፏል።
“በኅብረት የጠነከረች፣ በብዝኃነት የተዋበች ኅብረብሔራዊት ሀገር – ኢትዮጵያ!” በሚል ባስተላለፈው መልዕክትም፤ ኢትዮጵያችን መልከ ብዙ ናት፡፡ ሀገራችን ብዝኃነት ያደመቃት፤ ኅብረት ያጠነከራት ኅብረብሔራዊት ሀገር ናት ብሏል።
ኢትዮጵያ በሁሉም አውዶች አሸናፊ እንድትሆን፣ ከመበታተን ይልቅ መሰባሰብ፣ ከመገፋፋት ይልቅ መከባበርና እኩልነት፣ ከግጭት ይልቅ መቻቻልና ለሐሳብ ልዕልና ቅድሚያ በመስጠት አንድነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:¬-
በኅብረት የጠነከረች፣ በብዝኃነት የተዋበች ኅብረብሔራዊት ሀገር – ኢትዮጵያ!
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡
መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
ኢትዮጵያችን መልከ ብዙ ናት፡፡ ሀገራችን ብዝኃነት ያደመቃት፤ ኅብረት ያጠነከራት ኅብረብሔራዊት ሀገር ናት፡፡ ብዝኃነታችን መገለጫችን፤ አንድነታችንም የጥንካሬያችን ምንጭ ነው፡፡ በየዘመኑ ያጋጠሙንን ሀገራዊ ፈተናዎችን በአንድነት ቆማን መሻገር መቻላችን አንድነታችን የጥንካሬያችን መንጭ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ይህ የጥንካሬያችን ምንጭ የሆነው አንድነታችን አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን እኩልነትና ፍትሓዊነት የሀገረ መንግሥት ግንባታችን መሰረቶች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
በመሆኑም የዘንድሮውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ስናከብር፤ ሀገራዊ አንድነታችንን ከብዝኃነታችንና ከእኩልነታችን አንፃር መመልከት ይገባናል፡፡ የእኩልነትና የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ሀገራዊ አንድነታችንን የበለጠ ማጠናከር ምርጫ ሳይሆን የህልውናችን ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሁሉም አውዶች አሸናፊ እንድትሆን፣ ከመበታተን ይልቅ መሰባሰብ፣ ከመገፋፋት ይልቅ መከባበርና እኩልነት፣ ከግጭት ይልቅ መቻቻልና ለሐሳብ ልዕልና ቅድሚያ በመስጣት አንድነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም፡፡
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ እኩል ባለቤት ነው፡፡ እኩል ኃላፊነትም አለበት፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የተደነገጉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የእኩልነት መርሆችም፤ እያንዳንዳችን ለሀገራችን እኩል ባለቤትና እኩል ኃላፊ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡትን የእኩልነት መርሆዎች እውን ለማድረግ መንግሥት የሕዝቦችን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ሁሉ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከርና የእኩልነት መርሆችም የበለጠ እንዲተገበሩ ነጠላና ከፋፋይ ትርክቶችን በታላቁ ሀገራዊ ትርክት መተካት ያስፈልጋል፡፡ ከነጠላ ትርክቶች ተላቅቃን ፤ ብሔራዊ ትርክትን ማድመቅ ያስፈልጋል፡፡
ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ግንባታ የምናደርገውን የጋራ ርብርብም በስፋት ማስቀጠል በእኩልነት መርህ ላይ ለተመሠረተው ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን በእጅጉ ሊጠናከር ይገባል፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሁሉ አንድነታችንን በሚያጠናክር አግባብ በንግግር እና በውይይት እየፈቱ መሄድ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆን አለበት፡፡
በፈተና ውስጥም ኾነን ስኬት እያስመዘገብን፣ ሀገር እየገነባንና ትውልድ እያሻገርን በመተባበር፣ በመከባበርና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አብሮነታችንን እናስቀጥላለን! ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት!!